ይድረስ ለተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች (ክፍል ፪ )
ጥቅምት ፪ሺህ ፪
ምዕራባዊ አገራችን በማን አለብኝነት ተቆርሶ ለሱዳን መሰጠት ላይ ስለመኾኑ
በመስከረም ወር ጠንከር ያለ ደብዳቤ ስለዚሁ አስጊ ጉዳይ ጽፌላችሁ ነበር። እንደዚያ ዓይነት ጠጣር መልዕት እንዳስተላልፍ ያስገደደኝ የብዙሃን ወገኖች ጭንቀትና ስጋት ተጋሪ በመኾኔ ባለኹበት ኹናቴ ደግሞ እንደተጨነቁ ከመታፈን የዳንሁ ስለኾነ በዚሁ ዕድል ባልጠቀም የኅሊናን ወቀሳ ስለማልችለው ነበር።
እንደገና እንድመለስበት ያስገደደኝ በእናንተ በኩል (ሌላ ለማን አቤት ልበል! ?) ከዚህ ማስታወሻ በኋላ በበኩሌ ምንም የሚስብ ነገር ከእናንተ ባለማግኘቴ ነው።
“…እናንተም እንደገዢዎቻችሁ ‘ጭጭ…’ ማለታችሁ ነው። ከኃላፊነትም አታመልጡም። ስለዚህ፦
ሀ) አገር ውስጥ ያላችሁት፦
- ባስቸኳይ ተሰባስባችሁሕዝቡን ለሰላማዊ ሠልፍ ጠርታችሁ ዕውነቱን ማስረዳት ግዴታችሁ ነው።
- ሳትነግሩት ቀርታችሁ፦ነገ በዚህ ምክንያት ጦርነት ሲነሳ ሕዝቡንና ልጆቹን ለጦርነት ተነሱ ብትሉ “ ለምን?” ቢሏችሁ፦ ምን ትመልሳላችሁ?! ጶለቲከኞች
እንኳን መልስ ታጣላችሁ ማለት ተላላነት ሳይኾን አይቀርም።
- ርግጥ፦ የፖለቲካ ቡድኖች ሁላችሁም በአንድ መቆም እንደሚቸግራችሁ ገባኛል። በጥቃቅን ነገር የምትለያዩት ግን እሱን ወደኋላ አድርጋችሁ በአንድ መሠለፍ የአባት አያቶቻችሁን ጋሻ ወደ ማንሳቱ ያቃርባችኋል። እነዚያኞቹ ይለይላቸው።
ለ) ውጭ አገር ያላችሁት ፖለቲከኞችም ይህን መንፈስ ተከትላችሁ ማድረግ የሚገባችሁን እንደምታደርጉ ተስፋ አለኝ። እዚህ ላይ ደጋፊ መገናኛ ብዙዎችን ሁሉ ለዚህ ቅድሚያ ቢሰጠው ሳይጠቅም ይቀራል?
ሐ) ኹላችሁም ግን ለተባበሩት መንግሥታት፦ ለአፍሪካና
ለአውሮፓ ኅብረቶች እንዲሁም ለአረብና ለእስያ
አገራዊ ድርጅቶች መጻፍ ብቻ ሳይኾን የሕዝብን
ፊርማዎች በማሰባሰብ ለአካባቢያችን ሰላም መደፍረስና
መተላለቅ ከዝምታ ርቀው ይኽን እሳት ሳይቀጣጠል
በቅጠል እንዲያጠፉት እንረባረብ።
ጽሑፌ ድርቅርቅ ቢል ከአረረ አንጀት ከደበነ ቆሽት ከተበሳጨ መንፈስ መኾኑን ከመግለጽ አልፌ የማንንም የቅርታ አልጠይቅም።”
የሚል ነበር!!
በእናንተ በኩል የወገንን ስጋትና ጥያቄ ላስተጋባላችሁ ጥያቄ ምንም የተጨበጠ ርምጃ ባለመታየቱ ነው። ይኽን ስል በዘንድሮው የምክር ቤቱን መክፈቻ ንግግር በተመለከተ የ”ማሻሻያ ሃሳብ መጨመሪያ ላይ” ማንሳታችሁን ባለመዘንጋት ነው።
የተሰጣችሁ መልስ ለእኔ እንደተሰማኝ ንቀት በተሞላበት መንፈስ ‘እንዴት ትጠይቁኛላችሁ?’ በሚል ዓይነት “ ባስተዳደር በአድሚኒስትሬሽን ሥራው እየተሠራ ነው”
በመልሱ ላይ መመለስ ዕድል ስላልነበራችሁ አንጀታችሁ እያረረ በዝምታ ከማለፍ ሌላ አማራጭ አልነበራችሁም።
“ በአስተዳደር በአድሚኒስትሬሽን ሥራው እየተሠራ ነው” የተባለውን እኔ እንደተረዳሁት አዋሳኝ “ክልሎች ሉአላውያን እንደመኾናቸው ከግዛታቸው እንደፈለጉ ( በትዕዛዝ ) ቆርጠው ከሰጡ በኋላ ‘ይኽ የክልሎች ሥልጣን ነው!” ሊባል መቻሉን ከኔ እናንተ ታውቃላችሁ!!!
አማራጭ ማጣቱ ግን ምክር ቤት ተብዬው ውስጥ እንጂ እውጪ እንደዚያው የታፈናችሁ ስላልመሰልኝ በድጋሚ ከላይ ያሳሰብኋችሁን መንገዶች ካልሠራችሁባቸው ከሕዝብና ከታሪክ ተወቃሽነት ቀድሞ በሚቀጥለው ምርጫ ሕዝቡ “ አገሬ ተቆርጣ ስትሰጥ “አቋቁሙኝ” እንኳን ላላለ ድምጼን የምሰጠው ምን እንዲጠቅመኝ ነው?” ቢል ወይም አንጀቱ ያረረ አንዳንድ ጎጂ ቅመሞችን ጨምሮ ሕዝቡን እንዲህ ቢገፋፋው ጉዳቱ አይከፋም?
በድጋሚ የብዙሃንን አዘንና መከፋት በተቻለኝ አለሳልሼ አቅርቤላችሁአለሁ። “ለአንበሳ አይመትሩም ለብልኅ አይመክሩም”ን አልፌም እዚህ ደርሻልሁ። ፈረሱም ሜዳውም እናንተው ዘንድ ነው!!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያችንን ይርዳ! እኛም እንርዳት!!
ኮማንደር አሰፋ ሰይፉ
ዋና ገጽ