ወደ ተቀደሱ ፍልሚያዎች ድረ ገጽ እንኳን ደህና መጡ!    If you can not display Amharic fonts in this site please download Geez fonts here

 

ዋና ገጽ

አላማችን


አንገብጋቢ ፍልሚያዎች

ሊያገኙን ሲፈልጉ

ምርጫ 2002 ላገር ሞት ወይ ሽረት!

                    

የአዛውንት ያለህ! ለአገር ድረሱ ፦

መስከረም ፪ሺህ ፪

አምና ነሐሴ መጨረሻ ላይ የዓለም ዐቀፍ የኢትዮጵያውያን ሴቶች መወያያ መድረክ (ፓል ቶክ) ላይ የማውቀውን አካፍላቸው ዘንድ ጋብዘውኝ፡ያው የ ኹላችንም ምጥ በኾነው የአገር ጉዳይ ላይ ብዙ አሳቦች ከተለዋወጥን በኋላ፦ ከጋባዦችም ከተሰብሳቢዎችም “አዛውንት አመራር ስጡን!” የሚል ትዕዛዝ መሰል ጥያቄ ወይስ ፍልሚያ ልበለው፦ ግሎ ተደጋገመ።

እኔም አዛውንት ካገራቸው ጉዳይ ርቀው ወይም ለመራቅ ፈልገው ሳይኾን ከየአደባባዩ የተለዩት ደርግ ከመጣ ጀምሮ ስድቡና ውርደቱ ስለበዛባቸው መኾኑን በምሳሌዎችና ማረጋገጫዎች ላቀርብ ሞከርሁ።እንዲያውም አንዳንድ ሽምግልና ያልደረሱትም ከየመድረኩ የተለዩት አዛውንት ሲዋረዱ አናይም/አንሰማም በማለት እንደኾነም ላስታውስ ሞከርሁ።

ተሰብሳቢዎችና ሰብሳቢዎች ግን ሊቀበሉኝ አልፈለጉም።እንዲያውም ያልኹት ዕውነት ዕንደነበር አምነው ያነዬ ይኽን አድራጊዎች ግራ ክንፎች እንደነበሩ አረጋግጠው ‘ አኹን እኮ ይኽን ያደርጉት የነበሩት በዚያን ዕድሜና ደረጃ ላይ አይደሉም። በማለት “ አዛውንት አመራር ሰጥተው ይኽች አገር ከወደቀችበት እንድትወጣ ማድረግ አለባቸው!” የሚል የፍጹም ኢትዮያዊነት ጭንቀት የተሞላበት እልህ መሰል ጥያቄአቸውን/አደራቸዉን ጫኑብኝ።

እዚህ ላይ “ አዛውንት” ማለት ምን ማለት ነው ብዬ አለቃ ተክለወልድን ጠየቅኋቸው።ርሳቸውም “ ጨዋ ማለት ነዋ!”  
ብለው ቀጥ አሉ፡፤ እኔም መች በዚህ እንላቀቃለን ብዬ “ ጨዋ ማለትስ?” አልኋቸው። ርሳቸውም ፈታ አሉልኝ። ላካፍላችሁ፦ “ጨዋ ማለትማ” አሉ አለቃ “ልሌላውን ትተን የምትፈልገውን ልንገርህ።ጨዋ ማለት ዐዋቂ፦ አዛውንት፦ሽማግሌ፦ አስታራቂ፦ ገላጋይ…ጨው ምግብን እንደሚያስማማ ጨዋም መክሮ ዘክሮ አንተም ተው አንተም  ተው ብሎ የተጣላን ያስታርቃል።በጠብ የተለያየውን በፍቅር አንድ ያደርጋልና ጨው እንደማለት ጨዋ ተባለ። ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን”እናንት የምድር ጨው ናችሁ” እንዳለ ማቴዎስ ፭ ፲፫ን ጠቅሰው አስተማሩኝ።

እኔም በተጣለብኝ አደራ መሠረት ግዳጃችንን እንድንወጣ አገር በበለጠ እንዳትከፋፈል ወገንም እንዳይተላለቅ እባካችሁ ፈቃድኝነታችሁን አስታውቃችሁኝ እየተመካከርን ግዳጃችንን እንወጣ። እስክዚያው፡ የተለያዩ ፍልሚያዎችን ለመንደርደሪያ አቀርባለሁ። አንድዬ ይርዳን!


ዋና ገጽ