ኢትዮጵያችን ምን ዓይነት ኹናቴ ላይ ነች?
(ክፍል ፩)
መስከረም ፪ሺህ ፪
ብዙዎቻችን ላይ-ላዩን ማወቃችን ባይካድም ለግዴታችን ውሳኔ ይረዳን ዘንድ የወደቀችበትን አዘቅት፦የተጋረጡባትን ጠንቆች፦ የቀበሩባትን ፈንጂዎች፦የቆፈሩባትን ጉድጓዶች ወዘተ መዳሰሱ ይጠቅማል። ይበልጥ ግን የሚያስፈልገን ይህን ኹሉ የፈጸሙብንና የሚፈጽሙብን እነማን እንደኾኑ ማወቅ የሚገባንና የሚጠቅመን ይመስለኛል። እንደቅምሻም ቢኾን፦ እነሆ!
‘ ነገር ከሥሩ ውሃ ከጥሩ’ እንደሚባል፦ከዘመነ-መሳፍንት ብንጀምር፦ መሳፍንት ለ፸ ዓመታት ያህል ሲገዙ በደካማዎች ንጉሦች ስም ነበር በራሳቸው አልነበረም።አገራቸውንና የአገራቸውን ሕዝብ ያውቁ ነበርና!
እዚህ ላይ አውሮፓውያን አፍርሪካን በርሊን ላይ በ፲፰፻፹፬ በተቀራመቱበት ወቅት ኢትዮጵያችንን ለሦስት (እንግሊዝ፦ ፈረንሳይና ኢጣሊያን ) ተመኝተዋት እንዲያውም በወረቀት ላይ ተካፍለዋት ነበር። እምዬ ምኒልክ ግን ‘ ምን አግብቶህ በአገሬ!’ ብለው አስቀሩት። በዚያን ዘመን አንድ እንግሊዛዊ አገር ጎብኚ አፍሪካንና ሌሎች አገሮችንም ጎብኝቶ ጥንታዊቷንና ባለታሪኳን ኢትዮጵያን አይቶ ሲጽፍ ‘ በየሄድሁበት ጥቁሮች ለነጮች ሲሠሩ(ሲያገለግሉ) አየሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ነጮች ለጥቁሮች ይሠራሉ’ ብሎ ጻፈ። ልብ ማድረግ እንጀምር፦፡
ከዚህ ጀምሮ ኢትዮጵያዊነት (ኢትዮጵያኒዝም) በቅኝ ግዛት ቀምበር ስር ለሚቃትቱት ተስፋና ጉልበት ኾናቸው። ከሰሀራ ደቡብ ያሉት አገሮች ‘ኢትዮጵያዊነት’ን አንግበው እስከ ደቡብ አፍሪካ ድረስ ‘ የቅኝግዛትን መሠረት አናጉት’ አሉ አንዳንድ ጸሐፊዎች። እዚህ ሥፍራ የተቀጣጠለው የ’ኢትዮጵያዊነት’ መንፈስ አትላንቲክን ተሻግሮ ካሪቢያንና አሜሪካንም ውስጥ እነማርከስ ጋርቢን አስነስቶ ለብዙ የነጭ መንግሥታት ራስ ምታት ሳይኾን አልቀረም። በአሜሪካን የነጻነት ጦርነት ጊዜ በ ‘ኢትዮጵያ ባታሊዮን’? ስም የአፍሪካ ልጆች ጂዮርጂያ ውስጥ ሳቫና እሚባል አካባቢ ተዘጋጅተው ግዳጃቸውን በጀግንነት እንደተወጡ አንብቤአለሁ።
‘ኢትዮጵያዊነት’ ያቀጣጠለውን የነጻነት እሳት ለማጥፋትና ቅኝ አገዛዝን አመቻችቶ ለማስቀረት ‘ኢትዮጵያዊነትን’ ላለማጥፋት አማራጭ አልነበራቸውም። ስለዚህ ኢትዮጵያን መግዛት፡ ዕቅዳቸውንም ዕውን ለማድረግ አድዋ ዘመቱብን።
አጼ ምኒልክ ዳግማዊ ምኒልክ ት.ቤትን ሲከፍቱ ከአውሮፓ መምሕራን ለመቅጠር ፈልገው እንዳልኾነላቸው ቢያውቁም ለአንዳንድ የሥልጣኔ በር ለመክፈቻ ቀ.ኃ.ሥ. እንደ አጼ ምኒልክ የአውሮፓን አገሮች በር ለማንኳኳት ሞክረው ሳይኾንላቸው ሲቀር ከጃፓን ጋር፦ የጥንት የንገሥታት አገሮች እንደመኾናቸው፦ በጋብቻ ጭምርም እንዲዛመዱ ለመዋዋል የውጪ ጉዳይ ሚንስትራቸውን ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴን ላኩ። ብልሁ ሚኒስትርም ፮ ወር ቆይተው ተልዕኳቸውን በስምምነት ደርጃ አሳክተው ተመለሱ። እንግሊዝ የዓለምን ፫/’፬ኛ የምትገዛበት ወቅት ስለነበር ጉዳዩን ደርሳበት ‘በአፍሪካ ውስጥ ሌላ ጃፓን እንድትነሳ አንፈቅድም’ ብላ አጨናገፈችው።
ከዚያ የኦስትሪያው ናዚ ባሮን ሮማን ፕሮችሃዝካ የሚባለው አዲስ አበባ በ፲፱፻፳፬ አካባቢ በቆንሲልነት ለ፪ ዓመታት ያኽል ቆይቶ የተባረረው
“ አቢሲኒያ የባሩድ በርሜል “ በሚል ርዕስ በጻፈው መጽሐፍ “ ከ፬ ዓመታት ጀምሮ የኢትዮጵያ ን. ነ. ቀ.ኃ.ሥ፦ ከጃፓን ጋር በቅርብ በመወዳጀት ከነጭ ዘር ጋር የሞት ሽረት ትግል ይዟል” ብሎ፦ “ይህ ከቀጠለ በነጮች ላይ የሚያስከትለውን ለመተንበይ ያስቸግራል፦” እያለ መርዙን በሰፊው ነዛው።ኢትዮጵያ ነጮች ላልኾኑት ሕዝቦች ኹሉ መሪ ልትኾን ትፈልጋለችም፦ ብሎ ይኽም ለነጮች ጥቅም ኹሉ እጅግ አስጊ ነው ብሎ አስበረገገብን። መጽሐፉም በአውሮፓ ቋንቋዎች ኹሉ ተተረጎመ።
ለዚህም መድሃኒቱ ኢትዮጵያን በዘር መከፋፈል ብቻ ነው በማለት። ‘የራስን መብት በራስ መወሰን’ የሚለውንም ፍልስፍና፦ እንዳንዳንድ ጸሐፊዎች፦በዓለም ላይ በመጀመሪያነት ተከለ። መጽሐፉም በዋና ዋና የአውሮፓ ቋንቋዎች ኹሉ ተተረጎመ። የኢጣሊያንኛው ትርጉም ስሙን “ አቢሲኒያ ጥቁሩ ስጋት ወይም አደጋ “ ኾኖ በእንግሊዙ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሆርና በፈረንሳዩ አቻው ላቫል ሴራ የዓለም መንግሥቶችን ( ሊግ ኦፍ ኔሽንስን) ውል አፍርሰው በኢጣሊያኖች በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. አስወረሩን።በሕግ የተከለከለውን መርዝ ሲያዘንብብን “ ቶሎ-ቶሎ ጨርስ!” ተባለ።
በ፪ኛው የዓለም ጦርነት ናዚዎችና አቅሲሶች ከምዕራብና ከምሥራቅ የነዳጅ ዘይት ማዕከል ወደኾነችው አረብ አገር ሲገሠግሱ ለዓላማቸው ማሳካት ያስገቧትን ኢጣሊያን ከኢትዮጵያ ማስለቀቅ ምርጫ የሌለው ጭንቀት ኾነባቸው። ለዚህም ከሎንዶን አስወጥተው ወደ ክፍለ-አገር የወረወሯቸውን ቀ.ኃ.ሥ.ን ይዘው ሱዳን አድርሰው፡ ‘ን. ነግሥትህን እናመጣልሃልን እያሉ ባይሮፕላን ወረቀታቸውን በአገራችን ላይ አዘነቡት። ሚኒሽርና ዲሞትፎር የሚባሉትንም ጠብመንጃዎች፡ ለአርበኞች፦ ለየባላባቱና ለታወቁ ሰዎች እንዲደርስ አደረጉ፡፤ ይህ ኹሉ ሲኾን ጃንሆይን ኢትዮጵያ-ሱዳን ጠረፍ ላይ በማስቀረት አገሪቱን ለመያዝ ያቀዱ መኾናቸውን ያወቀው በጃንሆይ የሚመራውን ጦር የሚያዝዘው ኮሎኔል ዊንጌት አገሪቱን ለመያዝ መፈልጋቸውን ዐውቀው፦ ለኢትዮጵያ ባላቸው ፍቅርና ክብር ምክንያት ሊዋጥላቸው ባለመቻሉ፦ ሊኖራቸው የሚገባውን መሣሪያ መንግሥታቸው ባይሰጣቸውም፦ን.ነገሥቱን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ገሠገሡ። አርበኛውም የእንግሊዝን ተንኮል ጠርጥሮ ን.ነገሥታችንን ካላመጣችሁ ለኛ ነጭ ነጭ ነው መለየት አንችልም ብለው ማስጠንቀቂያ ሰጠ።
እንግሊዞችም የዘመቱበትን ግዳጅ ላለመሰዋት፡ ሳይወድዱ ቢያስገቧቸውም፦ የደቡብ አፍሪካ ጦር ከጃንሆይ ቀድሞ አዲስ አበባ እንዲገባና እንዲቆጣጠር ተደረገ። የጃንሆይን ሃሞት አጥቅሶ ለመቅመስ ትኅትና በተሟላባቸው ቃላት፡ ጄኔራል ስመትስ፡ የጦሩ ዋና አዛዥ እርሱ ዘንድ ሄደው ያነጋግሩት ዘንድ ላከባቸው። ጃንሆይም ‘ይቺ ባቄላ ያደረች እንደኾን አትቆረጠምም’ እንደማለት ‘ጉዳይ ካላቸው ዐቃቤ-ሰዐት ይዘው ሊያነጋግሯቸው እንደሚችሉ’ መመለሳቸው ተነግሯል። ይህ የኾነው አገራችን በንግሊዝ ጦር በተያዘችበት፡ አንዲት ቤሳ በሌላቸው ጊዜ እንደነበረ ማስተዋሉ አይከፋም። ጃንሆይ የነበራቸው ትጥቁን ያልፈታ አርበኛ፡( ከንግሊዝ ጦር ጋር የሚወዳደር ባይኾንም) ከውርደት በመላቀቁ የፈነጠዘና በምንም ዓይነት ለዳግምኛ ውርደት የማይበገር ሕዝብ ነበር። ምንም ጓዳው ውስጥ ገብቶ ቢኾንም ከቆረጠ ሕዝብ ጋር መቆራቆሱ ውጤቱን ለመተንበይ የሚያስቸግር እንደነበር መገመቱ አያዳግትም። ዋናው ነገር ግን የእንግሊዞች ጦርነት ከጊዜ ጋርም ስለነበር ከመጀመሪያው እንደተጠቀሰ፡- አለመሞከራቸው ብልጠት ሳይኾን አልቀረም። መላ-ምቱን ልተወውና እንግሊዞች አብብደረጉብን ላይ ላተኩር በከፊልም ቢኾን።
በቀደምት፦አውሮፓ ውስጥ ከጀርመንና ከኢጣሊያን እንዳስለቀቋቸው አገሮች “ ነጻ ፈረንሳይ ነጻ ቤልጂም ወዘተ” ሳይኾን ያችን የታሪክ ንግሥት፦ያችን ነጻነትን ለሌላ ያተረፈች የነጻነት እመቤት፦ እናት ኢትዮጵያን “የተያዘች የጠላት ግዛት” ( ኦኪዩፓይድ ኤኒሚ ቴሪቶሪ) ብለው ሰየሟት። “ሊበሏት የሚፈልጓትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል” እንደሚባለው።በጥልቀት፦ በረቂቅነትና በዘዴ ከኹሉም በላይ ደግሞ በጎሣና በሃይማኖት ሊከፋፍሉ የሞከሩትን አክሽፈው ቀ.ኃ.ሥና አርበኞች ነጻነትዋን መለሱላት።ከዚያ በፊት ከእንግሊዝ ጋር የነበረውን ግብ-ግብ መዘርዘር ባይቻል እንኳን አንዳንዱን መጥቀስ የግድ ይላል፡ ትግላችን፡ ፍልሚያችን ከማንማን ጋር እንደኾነ ለማወቅ ያህል። አገርን እንደፈለገችው መከፋፈል ባይኾንላት እንኳን፦ ውጋዴንን ለሱማሌ፦ ቦረናን ለኬንያ፡ ጋምቤላን ለሱዳን ልታደርግ በቁርጥ ሞክራ ነበር። የቦረናና የጋምቤላ ሳይኾንላት ሲቀር በውጋዴን ላይ ከአሥራአንድ ዓመት በላይ አልፍታናለች። መጨረሻ ስትወጣም፡ “ታላቋ ሶማሊያ” የሚባል መርዝ ረጭታብን እስካሁን መዘዙ አልለቀቀንም።
የባሰ አለ፦ ጣሊያኖች በ ፭ ዓመታት ውስጥ ፋብሪካዎችን፦ ሐኪምቤቶችን፦ስልክ ቤቶችን፦ የውሃ ማስተላለፊያዎችን … ሠርተው ነበር። በዓመት ፮ሺህ መኪናዎችን የሚያድስ ትልቅ ጋራዥም ነበራቸው። በአፍሪካ ውስጥ ትልቁ የነበረው የዱቄት፦ የጥጥ ፋብሪካዎችም ነበሩ። በቀን ፬፻ ኪዩቢክ ሜትር ለሐኪም ቤቶች እጅግ አስፈላጊ የሚኾን ኦቅሲጂን የመሠራም ነበር፡፡ ሊሎች ፲፩ ልዩ ልዩ ፋብሪካዎችም እንደነበሩ አንብቤአለሁ።እነዚህን ኹሉ ነቃቅለው ወደየኮሎኒያቸው ላኩት።
በዘመኑ የነበሩትን ወገኖቻችንን ያንገበግባውቸው ከነበሩት ውስጥ ‘ ኮኔል’ የሚባለው ብዙ ፋብሪካዎችን ያቀፈ ድርጂት ጉዳይ ነው። ኮኔል የመብራት ኃይል ማመንጫ፦ የሳሙናመሥሪያ ፋብሪካ፦ የዲዝል የርሻ መኪኖችን መገጣጠሚያና ማደሻ፡ የውሃ ጉድጓድ መቆፈሪያ መሣሪያዎች፦አያሌ ከባድ የጭነት መኪናዎች ነበሩት ነበር። እንዲሁም የዘይት መጭመቂያዎች፦ ትላልቅ መጋዞችና የማዕድን መቆፈሪያዎችም ነበሩ።መረሳት የማይገባቸው ብዙዎች የመንገድና የድልድዮች መሥሪያ መሣሪያዎችና አራት ማተሚያ ቤቶች ውስጥ የነበሩትን መሣሪያዎች ኹሉ ዘርፈው እንደላይኛው ለየኮሎኒዎቻቸው አደሉ። ይኖሩበት ይመስል። ወገን የማተሚያ ቤቶችን ነገር በማጤን የተንኮሉን ጥልቀትና ስፋት ሳያመለክተን አይቀርም።
አኹን በቅርቡ የተለዩን ለርጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ የነበሩት የ፺፯ቱ ዓመት አዛውንት፤ ክ. አቶ ምናሴ ለማ እንዳስተማሩኝ፦ ከዚያን ጊዜ በኋላ እንኳን ነገሩን ሲያነሱት እምባ እየተናነቃቸው፡ “ የገባነው ባዶ ቤት ነው። ቅድሚያ የሰጠነው ለትምሕርት ነበር። መማርያ መጻሕፍትን አዘጋጅተን ትምሕርት ቤት ልንከፍት ስንል፡ ስናይ ወረቀት የለንም። ከየት እናምጣ ብለን ስንወያይ ግብጽን አሰብን። አገሩንም ቋንቋውንም ስለማውቅ እኔ ተላክሁ። አልነበረም። በማፈላለግ ብዛት ሕንድ ተገኘ። ወረቀቱ ሲገኝ ጦርነት ስለነበር ማምጫው ቸገረ። በኋላ ከንግሊዞች በማስፈቀድ ፵ ቶን ብቻ ልናስመጣ ቻልን።” አሉ።”ለማሳጠር ልለፈው። እንግሊዞች በመጨርሻ ሲወጡ ባለሥልጣኖች “ ዩ ሜይ ራይት ኦፍ ኢትዮጵያ አዝ ኧ ሶርስ ኦፍ ሰፕላይ ኦፍ ፕላንት ኦር መሺነሪ ” ሲሉ መግለጫ ለለንደን አስተላለፉ።
ወደ ኤርትራ ስንሄድ መኻል አገር የተፈጸምው ኹሉ ሲደገም ወደቦች ስላሉ ለወደቦች የሚያስፈልጉ ብዙና ዐይነተኛ መሣሪያዎችን አራቁተዋል። በመካከላኛው ምሥራቅ ብቸኛ የነበረውን ተንሳፋፊ የመርክብ ማደሻን ኹለት ግዙፎች የእቃ ማንሽዎችንም ዘርፈው ወደ ምሥራቅ ግዛቶቻቸው ልከዋል። እንዲሁም ደለል ጠራጊ መርከቦችን፦ ከ፫፻ በላይ የባቡር ፉርጎዋችንና በመቶዎች ኪሎሜትሮች የሚለኩ ሃዲዶችና ልዩ ጠንካራ ሽቦዎች እንዲሁም ብዙ ብሎኖች ወስደው እንደ ቀድሞው አድርገዋል። እዚህ የተጨመሩት ከመኻል አገር በእጅጉ የሚበልጡ ሕንጻዎችን ማውደማቸው ነው። ሐኪም ቤቶች ሳይቀሩ።
እንደመኻል አገር ኤርትራንም መዕራቡን ለሱዳን ሊቆርጡ ፈልገው ነበር። ለኢትዮጵያ ወደቦቹ ይበቃሉ እያሉ። ያራቆቷቸው ወደቦች!
ጣሊያን አገራችንን ስትይዝ በቀደምት ዕውቅናን ከሰጧት ውስጥ የመጀመሪያዋ አካባቢ የምትገኘው እንግሊዝ ስትኾን በጦርነት ላይ እያለች እንኳን ዕውቅናዋን አላነሳችም ነበር፤፤ ይኽን ኹሉ በትዝብት ማለፍ ይቻላል። በትዝብት ማለፍ የሚቸግረው ግን ጣሊያን ስትውጣ በብዙ መልክ ያራቆተችንን ነው። በተጨማሪ እንግሊዝ ኤርትራን በባለአደርነት ለ፲ አመታት ባስተዳደሩብት ወቅት ጣልያኖችን ነበር መልሰው ሥልጣን ላይ ያስቀመጡት። ይህም ጣልያን ከኤርትራ መውጣት ስለማትፈልግ ደጋፊዎቿን ለማበርክት ጭምርም እንዲረዳት ነበር። ውሳኔው ብሕዝብ ፍላጎትና ድምጽ ይኾን ነበርና! ከዚህም በላይ “እናት ኢትዮጵያ ወይ ሞት” ብለው የተንሱትን አገር ወዳዶች ለማዳከም ያልተቆፈረ ጉድጓድ አልነበረም። ከጉድጓዶቹ ውስጥ እነዚህን ጀግኖች በማሰር በማንገላታት ብቻ ሳይወሰኑ ለፖለቲካ ተቀናቃኝነት የፈጠሯቸው ፓርቲዎችም ነበሩ። እነዚህን ፍጥሮቻቸውን አንድ ደራሲ የሥልጠናቸውን ልክ ሲገልጽ ‘ እንደ እንዝርት አሾሯቸው ‘ ይላል። ሙስሊም ወገኖቻችንን በአጼ ዮሐንስ ጊዜ “ ለሰማይ ምሰሶ ለእስላምም መሬት የለው” በሚል መርህ ካልተጠመቃችሁ እየተባሉም ብዙዎች ወገኖቻችን በይበልጥ ወደ ሱዳን የተሰደዱበትን ሁናቴ እያስታወሷቸው “ በደምባራ ብቁሎ ቃጭል ተጨምሮ “ እንደሚባለው በቀጥታና ባሾሯቸው ቡድኖች አማካይነት ሴራውን ያጧጥፉት ነበር። ይህ የከሸፈው በእነ ኬኪያ ውንድማማቾችና ኢትዮጵያ ውስጥ ለብዙ ዘመናት ያለአንዳች አመሳሶ (ልዩነት)
በሠሩና በኖሩ ኤርትርውያን እስላሞች አሳማኝነት ነበር።
አንድ እንግሊዝ በቀኃሥ ዘመነ መንግሥት ስለዚሁ ሲጽፍ፡ ከአጼ ምኒልክ ዘመን ከተጻፈው ገነን አድርጎ ፦ ‘ በዓለም ውስጥ ኹሉ ጥቁሮች ለነጮች ይሠራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የኅይወት ቅንብር ተዟዙሮ/ተገለባብጦ ነጮች ለጥቁሮች ይሠራሉ።’ አለ።
ይህ ኹሉ ነጮችን እያባሰባቸው ሄደ እንጂ ገርገብ አላደረጋቸውም።
ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ከቅኝ ገዢዎች እንድትገላገል ያልሞከረችው ሳይኖር ከተገላገለችም በኋላ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲቋቋም በፈጸመችው መሪ ተጋድሎ ባሮን ፕሮቻዝካ “ የአበሲኒያ የመጨረሻ የነጭ ዘር የጠላትነት አላማ/ ግብ ለባለ ቀለማት የአፍሪካ ሕይዝቦች ኹሉ ( ኦል ዘ ከልርድ ፒፕለስ ኦፍ አፍሪካ) መሪ ለመኾን ነው።” ያለውን ዕውን የሚያደርግ አስመሰለ። የብዙ አፍሪካዊያን አገሮች ነጻ ሲወጡ የሰንደቅ ዓላማችንን ቀለማት በተለያዩ ቅርጻ-ቅርጽነትና ኅብረት የራሳቸው በማድረጋቸው የባሮኑ ትንቢት ብዙዎችን፡ የበለጠ አሳሰባቸው ልበል? ወይስ አስደነገጥቸው? ስለዚህ መለስ ሰንደቅ ዓላማችንን ሰድቦ ለመጣል ካልኾነም ለመለወጥ የታገለው የአስቀማጮቹን ዓላማ ለመፈጸም ነበር። ሳይኾንለት ቢቀር መኻሉ ላይ ለጠፈበት።ይህን ርዕስ ሳልዘጋ የሌሎች አውሮፓውያንን ሴራ ወድኋላ አስቀርቼው የአሜሪካኖችን በአንድ ዐረፍተ ነገር ልዝጋው።
፪ኛው የዓለም ጦርነት አልቆ አፍሪካውያንም የቅኝ ግዛት ቀንበርን አሽቀንጥረው መጣል ሲጀምሩ ከአንዳንዶቹ ለትምሕርት ዓሜሪካ የሄዱ ነበሩ።
አንድ የአሜሪካ የዉጭ ጉዳይ መለስተኛ ሹም ለመናገሻው ከተማ አቅራቢያ ከነበሩት ዩኒቨርሲቲ ወደ አንዱ በየወእሩ ሳያሰልስ እየሄደ የሚደጋግመው አንድ ነገር ነበር። ይኸውም አፍሪካ ከኹሉም ኋላ ቀር አህጉር መኾንዋንና በምሳሌነትም ኢትዮጵያን ጠቅሶ ምንም ጥያቄ ሳይቀበል መሄዱ ነበር።
ከብዙ መመላለስ በኋላ አንድ ቀን “ ጥያቄ አላችሁ ወይ ? “ ሲበግን የቆየው ኢትዮጵያዊ፡ ‘ልምንድር ነው፤ ኹል ጊዜ ኢትዮጵያን ለኋላ ቀርነት ምሳሌ የምትሰጠው? ቢለው በጮሌነት “ አንተን ፊትለፊቴ ስለማይህ ነው ሲል፡ በተመሳሳይ መልክ የበሸቀውና ኢትዮጵያ በአሉታዊ ስትነሳ ከሚንገበገቡት አንዱ የምዕራብ አፍሪክ ልጅ “ ለልማት የሚያስፈልጉ ቀድመ ኹኔታዎች ምንድን ናቸው?” ሲለው አሜሪካዊው ሹም ሳያወላውል፡ “ ጸጥታና መረጋጋት” መኾናቸውን ሳያወላውል ሲመልስ፦ ጠያቂው “ ታዲያ ከኢትዮጵያ የበለጠ ጸጥታና መረጋጋት ያለው ይት ነው?” ቢለው ዕውነቱን አፍርጠረጠው። እንዲ ሲል፦ “ እኛ አሜሪካውያን አንድ ስህተታችንን አንደግመውም። ኹለተኛ ጃፓን አፍሪካ ዉስጥ አንፈጥርም።”
ከማን ነበር ይኽን የሰማነው? ወገን የዚህን ስልት ረቂቅነት እንደሚያስተውል ተስፋ አለኝ። የሥነ-ኅሊና ጦርነቱ በኢትዮጵያውያን ላይብቻ ሳይኾን በአፍሪካውያን ላይም እንደነበር። ይህንንም ለኋላ እናቆየው።
በን.ነገሥቱ ዘመን ውስጥ ለውስጥ ብዙ ደባዎች ሲሠሩብን ቆዩ። የሶሻሊዝምና የካፒታሊዝም ፍጥጫ በመጠኑም ቢኾን ፋታ ሰጠን። ይኽም ሲባል አንዳንድ የእስልምና ተከታይ አገሮች ሙከራዎች አልነበሩም ለማለት ሳይኾን በን. ነገሥቱ ዘመን እምብዛም የሚያስደነግጡ አልነበሩም።ሶሺያሊስምም የራሱ ሚና ነበረው። በአኹኑ ጊዜ በሶሺያሊስት አገሮች በኩል የሚያሰጋ ስለሌለ ልለፈው።
በእስልምና ሃይማኖት በኩል የነበረው አደጋ መሰል ሙከራ በጀማል አብድል ናስር የስዌዝን ቦይ ከእንግሊዞችና ፈረንሳዮች መቀማትና የአረቦችን ብሔርተኛነት በቀሰቅሰበት ወቅት ነበር። ያም ቢኾን በመንግሥትና በአገር ወዳድ እስላም ወገኖቻችን ተቀጨ። በዚህ ሃይማኖት ነክ ስላለው ችግር በኹለትኛው ክፍል እንገባበታለን።
እድሜ ለደርግና ግራ ክንፎች በኢትዮጵያችን ላይ ያደቡባትና ያሴሩባት ኹሉ በ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. ቀን ወጣላቸው። አደባባይም ወጣ!
የኢትዮጵያ ሕዝብ የወከለው ያልመከረበትን ሕዝብም በሕዝብነቱ ያልተጠየቀውንና ያላጸደቀውን ግን ከላይ በተጠቀሱት ያለቀውን “ ሕገመንግሥት “ ተብዬውን ‘ጸደቀ’ ተብሎ ግብዣው ሲቀልጥ የአራት ዋና ዋና ምዕራባውያን አምባሳደሮች ሲነጋገሩ ከ ‘አርቃቂ’ ተብዬዎች አንዱ የሰማውንና ያካፈልኝን ሳካፍላችሁ በጥሞና እንድታጤኑት ከአደራ ጋር ነው።
ኹለተኛው፡ - ገና ነን
የመጀመሪያው- ምን ቀረን?
ሦስተኛው - አክራሪ እስላሞችን ማስገባት አለብን
አራተኛው - ጥሩ ብላችኋል ግን ይቀራል የኦርቶዶቅስ ቤተክርስቲያንን
በወንጌላውያን ማጥለቅለቅ አለብን
( ይኽን የነገረኝ ወዲያውኑ ተሰደደ - አኹንም ስደት ላይ ነው)
እንግዲህ ወገኖቼ፦ ባሮኑ በጎሣ መከፋፈልን ነበር የሰበከው ሌሎቹ የጨመሩትን ጨመሩ። ኢትዮጵያችን በስም እንጂ እንደ ሌሎች አገሮች “ ሉዐላዊት አገር” እንዳልኾነች ስንታችን እናውቃለን?”
ሉዐላዊነት ያለው ክልሎች ዘንድ ነው። አንቀጽ ፰ን ተመልከቱ።
ባጭሩም ቢኾን በታሪኩ ዓይን የገለጽኹላችሁ፦ ዘመቻ ሲኬድ ጠላትን ዐውቆ መኾን ስላለበት ነው።
በዚህ መነጽር ምርጫ ፺፯ አካባቢና በኋላ የተፈጸሙትን እናንተው አብላሉት። ከዚህ ወደ ግዳጃችን መሸጋገር እንችላለን? አንችልም!።
አኹንስ የትግራይ ነጻ-አውጪዎች ነን በሚሉት ከተያዝን በኋላ” ይህንን በ ፪ኛው ክፍል እንዳብሰዋለን። ለማስታወስ ያህል\፤- ያሁን ጊዜ በመኾኑ አንዳንዱን ማወቃችን አይቀርምና! ኾኖም ለማስታወስም ያኽል ቢኾን ይቀርባል።
ዋና ገጽ